ኮምፒተር የሰዉን ልጅ ህይወት ከቀየሩ እና እጅግ ጠቃሚ ከሆኑ የቴክኖሎጂ ግኝቶች መካከል አንዱ እና ዋኛዉ ነዉ፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኮምፒዉተር ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ የታወቀ ነዉ ይህ ሁኔታ ከተወሰኑ አመታት በፊት በቀላል ዋጋ አዲስ ኮምፒዉተር በተለይም ላፕቶፕ መግዛት ይቻል የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ዋጋዉ በመጨመሩ ምክንያት አዲስ ላፕቶፕ መግዛት ለአብዛኛዉ ሰዉ አስቸጋሪ ሁኗል፡፡ በመሆኑም ያገለገሉ ላፕቶፖችን መግዛት በብዛት የተለመደ ሁኟል፡፡ ይህ ከፍተኛ ገንዘብ አዉጥተን የምንገዛዉ ኮምፒዉተር አዲስ ባለመሆኑ ለብዙ ሰዉ ስጋት እና ጥርጣሬ የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ኪሳራ ላይ ሊጥል የሚችል በመሆኑ ከመግዛታችን በፊት ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡
ኮምፒዉተር ስንገዛ እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ማወቅ ተገቢ ነዉ
- ኮምፒዉተሩን የምንፈልግበት አላማ ወይም ልንሰራ ያሰብንበት ጉዳይ፡፡
የኮምፒዉተርን ዋጋ ከሚወስኑ ነገሮች መካከል አንዱ ኮምፒዉተሩ እንዲሰራ የታሰበለት አላማ ነዉ ይህም ኮምፒዉተር የሚኖረዉ የመስራት አቅም የሚወሰንበት አንዱ ምክንያት ነዉ፡፡ መሰረታዊ የኮምፒዉተር ስራዎችን ለመስራት ማለትም ለፅሁፍ አገልግሎት፣ ኢንተርኔት ለመጠቀም፣ ቪዲዮ ለማየት፣ ለማንበብ፣ Power Point ለማዘጋጀት የምንፈልገዉ ኮምፒዉተር እና ከፍ ያለ አቅም የሚፈልጉ ስራዎችን ለመስራት ማለትም ሶፍትዌር ለማበልፀግ፣ የግራፊክ ዲዛይን ስራዎችን ለመስራት፣ የአርክቴክት ስራዎችን ለመስራት፣ የ Video Editing የመሳሰሉ ስራዎችን ለመስራት የምንፈልገዉ ኮምፒዉተር የሚኖረዉ ዋጋ እና አቅም የተለያየ ነዉ፡፡ በመሆኑም ከምፒዉተር ከመግዛታችን በፊት በግልፅ ማወቅ ያለብን አንደኛዉ እና ቀዳሚዉ ጉዳይ ይህ ነዉ፡፡
2. Physical Appearance ዉጫዊ ይዞታ
የምንገዛዉ ኮምፒዉተር ዉጫዊ አካሉ ያልተጎዳ፣ ስክሪኑ ያልጠቆረ ወይም መስመር የሌለበት፣ ሙሉ የኪቦርድ ፊደላት፣ ቁጥሮች እና Functional key ያልጎደለ፣ ምንም አይነት ስብራት የሌለዉ እና ላፕቶፕ ከሆነ ደመግሞ በቀላሉ መታጠፍ መዘርጋት የሚችል፣ ማጠፊያና መዘርጊያዉ ላይ ምንም አይት ጉዳት የሌለበት መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም ላፕቶፕም ይሁን ዴስክቶፕ በምትገዙበት ወቀት በተለይም ላፕቶፕ ስትገዙ ስትከፍቱት (ሲነሳ) ምንም አይነት ድምፅ የሌለዉ መሆን፡፡ አለበት እነዚህን ችግሮች ችላ ብላችሁ የምትገዙት ኮምፒዉተር ብዙ ጊዜ ላትጠቀሙበት ወይም ለአላስፈላጊ ወጪ ሊዳርጋችሁ ይችላል፡፡
3. Processor (Corei2, Corei3, Corei5, Corei7)
የኮምፒዉተርን ስራ የመስራት አቅም, ፍጥነቱን እና ዋጋዉን ከሚወስኑ ነገሮች ዋነኛዉ የኮምፒዉተር ክፍል ፕሮሰሰሩ ነዉ፡፡ ከፍ ያለ ፕሮሰሰር ያለዉ ኮምፒዉተር እና ዝቅተኛ ፕሮሰሰር ያለዉ ኮምፒዉተር የመስራት እቅማቸዉ የሚወዳደር አይደለም፡፡ በመሆኑም የምንገዛዉ ኮምፒዉተር ከፍ ያለ ፕሮሰሰር ያለዉ ቢሆን ይመረጣል፡፡
4. Hard Disk
ሀርድ ዲስክ የኮምፒዉተራችን ዊንዶዉ (Operating System) እና የእኛን የግል መረጃዎች ወይም ፋይሎች በቋሚነት የሚቀበጥበት ቦታ ነዉ፡፡ ኮምፒዉተራችን የሃርድ ዲስክ መጠኑ በጨመረ ቁጥር ብዙ መረጃዎቸን ማስቀመጥ ያስችለናል፡፡ ሁለት አይነት ሃርድ ዲስክ አሉ የመጀመሪያዉ Hard Disk Drive (HDD) ይባላል የቆየ እና በብዛት ኮምፒዉተሮች እና ላፕቶፖች ላይ ይገኛል፣ ሁለተኛዉ Solid State Drive (SSD) ይባላል አዲስ የሃርድ ዲስክ ቴክኖሎጂ ሲሆን ይህን ሃርድ ዲስክ የሚጠቀሙ ኮምፒዉተሮች በጣም ፈጣን ሲሆኑ በዋጋም ከመጀመሪያዉ ይወደዳል፡፡ SSD ሃርድ ዲስክ ከፍጥነቱ ባሻገር በክብደቱ ቀላል እና ቢወድቅ በቀላሉ አይበላሽም፡፡ በመሆኑም ኮምፒዉተር በተለይም ላፕቶፕ ስንገዛ ሃርድ ዲስኩ SSD ቢሆን ይመረጣል፡፡
5. RAM (Random Access Memory)
ይህ የኮምፒዉተር ክፍል ኮምፒዉተራችን ስራ ስንሰራ ብቻ የሚጠቀምበት ክፍል ነዉ፡፡ RAM መጠኑ ከፍ ማለቱ ዋነኛ ጥቅሙ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ስራዎን መስራት እንድንችል፣ የተለያዩ አፕልኬሽኖችን እና ፋይሎችን ቶሎ መክፈት እንድንችል ያደርገናል፡፡ ከፍ ያለ RAM ያለዉ ኮምፒዉተር ሲከፍት እና ሲዘጋ እንዲሁም ስራ ስንሰራበት ፈጣን ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከፍ ያለ RAM ያለዉ ኮምፒዉተር መግዛት ለስራችን መቀላጠፍ አስፈላጊ ነዉ ከ 4GB RAM ያላነሰ ቢሆን ይመረጣል፡፡
6. Screen Size
የ Screen Size በተለያየ መጠን የሚገኝ ሲሆን በብዛት ገበያ ላይ የምናገኘዉ ከ14፣ 14.5 እና 15.6 ኢንች ሲሆን ከዚህ ከፍ ያለም ያነሰም መጠን ስክሪን ያለዉ ኮምፒዉተር እናገኛለን (ለላፕቶፕ)፡፡ ነገር ግን ስክሪናችን ቢበላሽ ወይም ቢሰበር ከላይ ከተጠቀሱት መጠን ዉጪ ያለዉ ስክሪን ገበያ ላይ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡
ለዴስክቶፕ ከ14 – 19 ኢንች መጠን ያላቸዉ ስክሪኖች ሲኖሩ እንአገልግሎታቸዉ ከፍ ያለ መጠን ያላቸዉ ስክሪኖች መግዛት እንችላለን፡፡
7. Battery Duration ( Battery Life Time) (ለላፕቶፕ)
የምንገዛዉ ላፕቶፕ በአንድ ጊዜ ቻርጅ ረጅም ጊዜ መስራት የሚችል መሆን አለበት ይህም ጥቅሙ ስራ እየሰራን መብራት ቢጠፋ ስራችንን በባትሪዉ ቻርጅ መስራት እንድንችል ያደርገናል፡፡
8. Brand (Manufacturer)
የምንገዛዉ ኮምፒዉተር ብራንድ ወይም አምራቹን መምረጥ በዋነኛነት የድርጅቱን በገበያ ላይ ያለዉን ተቀባይነት፣ የምርቱን ጥራት እና መለዋመጫወች በቀላሉ ማግኘት መቻላችንን ለማወቅ ይረዳናል፡፡ ለምሳሌ ከተወሰኑ አመታት በፊት Toshiba ላፕቶፕ በገበያ ላይ በስፋት ይሸጥ ነበር ነገር ግን በአሁኑ ሰአት አዲስ Toshiba ላፕቶፕ ማግኘት አስቸጋሪ ነዉ በሆኑም ያገለገለ Toshiba ላፕቶፕ ብንገዛ ከተወሰኑ አመታት በኋላ ለላፕቶፓችን መለዋወጫ ብንፈልግ ላናገኝ እንችላለን፡፡ ስለዚህ የምንገዛዉ ኮምፒዉተር በገበያ ላይ በስፋት የሚገኝ፣ መለዋወጫ በቀላሉ የምናገኝበት መሆን መቻል አለበት፡፡ ወጣ ያለ ብራንድ ነገር ግን የተሻለ ብቃት ያለዉ ኮምፒዉተር ብንገዛ ምን ችግር አለዉ ካልን? መልሱ ኮምፒዉተሩ ቢበላሽ መለዋወጫ በቀላሉ ላናገኝ እንችላለን ነዉ፡፡ በአሁኑ ሰአት ገበያ ላይ በስፋት የምናገኛቸዉ ላብቶፖች HP, Lenovo እና Dell ሲሆኑ ዴስክቶፕ ደግሞ Dell እና HP ናቸዉ፡፡

